ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ጠንካራ አደረጃጀትና የአሰራር ስርኣት እንዲኖራቸው ማድረግ ማህበረሰቡን በተሻለ መልኩ እንዲያገለግሉ ብቻ ሳይሆን እሴቶቹ ተጠብቀው እንዲቆዩ በማድረግ በኩል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገለጸ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በቀጣይ በሚያካሂደው የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ክልላዊ የአደረጃጀት ጥናት ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።
(ሆሳዕና፣ታህሳስ 5/2017) ፣ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ጠንካራ አደረጃጀትና ዘላቂ የአሰራር ስርኣትና ደንብ እንዲኖራቸው ማድረግ ማህበረሰቡን በተሻለ መልኩ እንዲያገለግሉ ብቻ ሳይሆን እሴቶቹ ተጠብቀው እንዲቆዩና ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ በኩል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
የክልሉ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በባህላዊ ፍርድ ቤቶች ዙሪያ በሚያካሂደው የአደረጃጀት ጥናት ዙሪያ ውይይት ሲካሄድ እንደተገለጸው ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለማህበረሰቡ ከሚያስገኙት ፋይዳ ባሻገር የህዝብ ባህላዊ እሴቶችና መገለጫ በመሆናቸው በዘላቂ አደረጃጀት ተጠብቀው እንዲቀዩ ማድረግ ያስፈልጋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ እንዳሉት ባህላዊ የዳኝነት ስርአቶች የየብሄረሰቡ ድንቅ እሴቶች ናቸው። ከዚህ መነሻም እነዚህ እሴቶች ለማህበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ብቻ ሳይሆን ተጠብቀው እንዲቆዩ ማድረግ ይገባል።
ተቋማቱ በመደበኛው ፍርድ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ የሀሰተኛ መረጃና የፍርድ ሂደት መጓተት ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ያላቸው ሚና እንዲጎለብት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል ።
ለዚህ ደግሞ ዘላቂ አደረጃጀት እንዲኖራቸውና ወጥ የሆነ የአሰራር ስርኣት እንዲከተሉ ማድረግ ወሳኝነት እንዳለው አቶ ኤርሲኖ ተናግረዋል ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊሲ ጥናት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አክመል መሀመድ በበኩላቸው ባህላዊ የዳኝነት ስርኣት በግብረ ገብ ትምህርት ታግዘው በማህበረሰብ ደረጃ የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመፍታት ለፍትህ መስፈንና ተደራሽነት መረጋገጥ ትልቅ ሚና ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል ።
ጥልን በዕርቅና ይቅርታ በማሻር፤ ፍቅርና ሠላምን ለማፅናት የቆሙና የሰዎችን ሰላማዊ ህይወት ማስተሳሰሪያ እሴት ናቸው ያሉት ዶ/ር አክመል ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ ግጭቶችና አለመግባባቶችን በመፍታት እርቅና ሰላም እንዲወርድና የሕዝቡ አንድነት እንዲጠናከር የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል ።
ማህበረሰቡም በራሱ ባሕል፣ ስርዓትና ዕሴት ጉዳዮቹ ታይተው በአካባቢው ባህልና ወግ መሰረት ውሳኔ እያገኘ እንዲሄድ የሚያግዙ ናቸው ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በተለይም ደግሞ ጉዳዮችን በማህበረሰቡ ባሕልና ዕሴት መሰረት የሚያስተናገዱ በመሆናቸው ፍትሕ እንዳይዛባ የማድረግ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከመደበኛው ስርኣት ጎን ለጎን ለህግ የበላይነት መረጋገጥ የራሳቸውን ሃላፊነት እየተወጡ በመሆኑ አደረጃጀትና አሰራር መዘርጋቱ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸውም አክለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ከቱባ ባህልነታቸው ባለፈ በራሳቸውም ሆነ መደበኛ የፍትህ ስርኣቱን በማገዝ ለፍትህና መልካም አስተዳደር መስፈን ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል ።
ከዚህ መነሻ ዘላቂ አደረጃጀትና አሰራር እንዲኖራቸው በማዕቀፍ መደገፍ፣አቅማቸውን ማጎልበት፣የስልጣን ወሰናቸውን በአግባቡ ለይቶ ማስቀመጥና ያሉባቸውን ክፍተቶች መቅረፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በተለይም ዘላቂ ቁመና፣ የአሰራር ስርኣትና በህግ የተደገፈ አደረጃጀት እንዲኖራቸው፣ተቋማዊ መልክ እንዲይዙ፣ደረጃውን የጠበቀና ወጥነት ያለው አሰራር እንዲኖራቸውና የተሟላ እውቅና እንዲያገኙ ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
ተቋማቱ ህግን በማስከበር የማህበረሰብን ደህንነት በማረጋገጥና የሰላም እሴት ግንባታን በማገዝ በጥቅሉም ለህግ የበላይነት መረጋገጥ በኩል ያላቸውን ሰፊ ሚና ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባም ጠቁመዋል ።
እነዚህ አጋዥ ተግባራት የባህል ፍርድ ቤቶች ሚናቸውን በአግባቡ እየተወጡ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረውም ተብራርቷል።
በመድረኩ ጥናቱን በሃላፊነት የሚመራ ከተቋማት፣ባለድርሻ አካላትና ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጣ አብይ ኮሚቴ ተቋቁሟል።
046-55-62-112




