ህብረተሰቡ በፍትህ ስርአቱ ላይ አመኔታ እንዲኖረው ቅንጅታዊ አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ
(ህዳር 4/2017) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የዳኝነት እና የፍትህ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የተዘጋጀ የምክክር መድረክ ተጠናቀቀ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ እንደገለጹት በፍርድ ቤቶች እና በፍትህ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ላይ የሚስተዋለው መሰረታዊ ችግር እንዲፈታ መስራት ይገባል ብለዋል።
ከክልል ጀምሮ ያለውን የፍርድ ቤቶች እና የፍትህ ተቋማት ላይ የሚስተዋለውን የአሰራር ጥሰት በማሻሻል የህዝቡን የፍትህ ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ህዝቡ በተቋማት ላይ እምነት እንዲያጣ ያደረጉ ምክንያቶችን መፈተሽ አብይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም አፈ ጉባኤዋ አስረድተዋል።
የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጥባቸው ዘርፎች ላይ የትራፊክ ፖሊሶች የስነ ምግባር ብልሽት የህዝቡ የቅሬታ ምንጭ መሆኑንም አብራርተዋል።
ከዳኝነት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ስራቸውን በታማኝነት የሚያከናውኑ ዳኞች የመኖራቸውን የተናገሩት አፈ ጉባኤዋ የስነ ምግባር ጉድለት ያለባቸው ዳኞች ስለመኖራቸውም ጠቁመዋል ።
በአካባቢ፣በጎሳ፣በገንዘብ በሀይማኖት እና ተዛማጅ ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ የሚስተዋሉ የፍትህ ስርአት መጓደል ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ዋና አፈ ጉባኤዋ አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ እንደገለጹት ፍርድ ቤቶች እና የፍትህ አካላት
በዲሞክራሲ፣በመልካም አስተዳደር እንዲሁም በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ የላቀ ሚና አላቸው ብለዋል።
የፍትህ ተቋማት ለህዝቡ የሚሰጡትን አገልግሎት በገለልተኛነት በፍትሀዊነት እና ተአማኒነትን መሰረት ባደረገ መልኩ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል።
ከፖሊስ፣ከዳኞች እንዲሁም ከአቃቄ ህግ አንጻር የሚስተዋሉ የስነ ምግባር ችግሮችን ለመለየት ተከታታይ ህዝባዊ ውይይት በማካሔድ እንደሚገባም አቶ አንተነህ ተናግረዋል ።
የተጠያቂነት አሰራር በመተግበር በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅም ኃላፊው አሳስበዋል።
ባለፈው በጀት አመት ክልሉን ለማተራመስ የተከፈቱ ሀሰተኛ ማህበራዊ ትስስር ሚዲያዎች ላይ ክትትል በማድረግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም የጥላቻ ንግግር በሚያሰራጩ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ተገቢ ስለመሆኑም አቶ አንተነህ አብራርተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት በፍትህ ተቋማት የተጀመረው ቅንጅታዊ ስራ ቀጣይነት ማረጋገጥ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ባለፉት አመታት ከማዳበሪያ እዳ አመላለስ ጋር ተያይዞ የተሰሩ ስራዎች በፍትህ ሴክተሩ የተቀናጀ ስራ መሆኑንም አቶ ኡስማን ተናግረዋል።
የተወረሩ የወል መሬቶችን ስርዓት ማስያዝ ለሰዎች እና ለእእስሳት ህይወት የጤና ጠንቅ የሆኑ ህገወጥ መድሀኒት ቁጥጥር ላይ በትብብር መስራት እንደሚገባም ሀላፊው ጠቁመዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ እንደገለጹት የፍትህ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር መጎልበት በዘርሩ የሚካሔደውን ሁሉን አቀፍ ጥረት ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል።
በክልሉ ሰላምን ልማትን እና ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አቶ ኤርሲኖ በንግግራቸው አመላክተዋል።
ተቋሙ የተሰጠውን ስልጣን እና ኃላፊነት መሰረት በማድረግ የህዝብ ውክልናን ባገናዘበ መልኩ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።
ነጻነት ከተጠያቂነት ጋር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ የህዝብን አመኔታ በሚሸረሽሩ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ዳኞች ገለልተኛ ሆነው ለህዝብ የሚሰጡትን አገልግሎት በተገቢው መንገድ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የምድብ ችሎት ተደራሽነትን በማስፋፋት ህብረተሰቡ ከምርት ተግባሩ ሳይነጠል አገልግሎት የሚያገኝበትን ስርዓት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።
046-55-62-112




