Skip to main content

‎የፍትሕ ሥርዓቱን ነፃ ገለልተኛና ጥራት ያለው ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፦​ አቶ ኤርስኖ አቡሬ‎

‎ጥቅምት 2019 

‎የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዞንና ከልዩ ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመራሮች ጋር የ2019 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸምና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ለይ የውይይት መድረክ ተካሄዷል።

‎​በመድረኩ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤርስኖ አቡሬ እንደተናገሩት የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የዜጎች መብት እንዲጠበቅ ፍርድ ቤቶች ነፃ፣ ገለልተኛና በሕግ ብቻ የሚመሩ መሆን አለባቸው ብለዋል።

‎አገልግሎታችንን ይበልጥ የተሻለና ጥራት ያለው ለማድረግ እየሰራን የነበረውን ጥረት ይበልጥ ቀጣይነት እንዲኖረው ሁላችንም አጠናክረን መስራት ይገባናል ሲሉ አቶ ኤርስኖ አቡሬ ተናግረዋል።

‎አቶ ኤርስኖ አቡሬ አክለውም የዳኝነት አገልግሎቱን ይበልጥ ግልጽ ቀልጣፋ ተደራሽ እና ተገማች በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነትና እርካታ ማሳደግ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

‎በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዳኝነት አገልግሎትን በማስፋፋት የፍትሕ አሰጣጡን ቀልጣፋና ከእንግልት የጸዳ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

‎ብልሹ አሠራርና ሙስናን በመከላከል የርቀት ችሎቶችን አጠቃቀም አዲሱን የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ እንዲሁም የፕሮቶኮል አያያዝ ረቂቅ ሰነዶችን በቁርጠኝነትና በቅንጅት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።

‎​ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናት የባህላዊ ዳኝነት ሥርዓት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ሥርዓት ከሕጋዊ ማዕቀፍ ጋር በማቀናጀት ከዘመናዊው የፍትሕ አሰጣጥ ጋር በጋራ መምራት እንደሚያስፈልግ ፕሬዝዳንቱ አጽንኦት ሰጥተውበታል።

‎በመድረኩ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ እንዳርጋቸው ይድነቃቸው እንደገለፁት ሕገ-መንግሥቱን ባከበረና ግልጽነት ባለው አሠራር ዜጎች የሚገባቸውን ፍትሕ እንዲያገኙና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።

‎ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም የዜጎችን የፍርድ ቤት ቅሬታዎች በወቅቱ በመመርመርና ፈጣን ምላሽ በመስጠት የሕዝብን እምነትና እርካታ ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

‎በመድረኩ የዞንና የልዩ ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶችና ምክትል ፕሬዝዳንቶች የተገኙ ሲሆን፤ ከተሳታፊዎቹ ሰፋ ያሉ ሐሳቦች ቀርበው ፍሬያማ ውይይት ተካሂዷል።

Image
የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤርስኖ አቡሬ